የአርጡማ ፉርሲ ወረዳ የመስህብ ቦታዎችና ታሪካቸዉ
መግቢያ
አርጡማ ፉርሲ ወረዳ በኦሮሞ ብሔረሰብ ከሚገኙ ወረዳዎች አንዷ ናት፡፡ ወረዳዋ በዙሪያዋ ከሚገኙ በሰሜን ከደዋ ጨፋ ወረዳ፣ በምስራቅ ከአፋር ክልል፣ በምዕራብ ከአንፆኪያ ገምዛ ወረዳ እና በደቡብ ከጅሌ ጥሙጋ ወረዳዎች ጋር ትዋሰናለች፡፡ ከአዲስ አበባ በሰሜን አቅጣጫ 300 ኪ.ሜ ርቀት፣ ከዞኑ ዋና ከተማ በሰሜን አቅጣጫ 25 ኪ.ሜ ርቀት እንዲሁም ከክልሉ ዋና ከተማ በምስራቅ አቅጣጫ 580 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ የመሬት አቀማመጧ 28.5% ተራራማ፣ 38% ሜዳማ፣ 6.6% ሸለቆአማ፣ 4.4% ረግጋማ እንዲሁም 22.5% ወጣ ገባ ነዉ፡፡ የአየር ንብረቷም ቆላ 76%፣ ወይና ደጋ 24% ነዉ፡፡
በዉስጧ የተለያዩ ሀይማኖት ተከታዮች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም 97% እስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ሲሆኑ የተቀሩት 3% ክርስቲያንና ሌሎች ሀይማኖት ተከታዮች ይገኙበታል፡፡ ግብርና የወረዳዉ ጀርባ አጥንት በመሆኑም አብዛኛዉ ህዝብ 89% የሚተዳደረዉ በዚህ ክፍለ ኢኮኖሚ ሲሆን የተቀሩት 11% በመንግስት ስራና በንግድ ስራ የተሠማሩ ናቸዉ፡፡ ወረዳዉ 24 የገጠር ቀበሌዎችና 1 የከተማ ቀበሌዎች አቅፏል፡፡ በትምህርት መስክ 49 አንደኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ሶስት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ አንድ መሰናዶ ት/ቤትና አንድ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ት/ቤቶች ይገኛሉ፡፡ በጤናዉ ዘርፍ 22 ጤና ኬላዎች እና 6 ጤና ጣቢያዎች ተገንብተዋል፡፡ የህዝብ ብዛቷም ወንድ 54204 ሴት 55477 ድምር 109681 ናዉ፡፡
በሌላ በኩል ወረዳዉ የራሱ የሆነ ሰፊ ታሪክና ባህል ያለዉ ሲሆን በዉስጡም ብዙ ህዝቦች የሚኖሩ ሲሆን ባብዛኛዉን የኦሮሞ ብሔር የሚኖርበትና የአማራ ብሔርም በታሪክ ሲነገር ከ50 አመታት ወዲህ ወደ ወረዳዉ የተቀላቀለ ብሔር ነዉ፡፡ በወረዳዉ ናሆሌ፣ አማሮ፣ ጃርሶ፣ ዱበና፣ ገላን፣ ሀሪሮ፣ አባዶ፣ ጃሌ፣ ማሩታያ፣ ገለሻ፣ ወዘተ ጎሳዎች ባብዛኛዉን በወረዳዉ ዉስጥ ይኖራሉ፡፡
የወረዳዉ አሰያየም
አርጡማ ፉርሲ ወረዳ ቀደም ሲል በአገራችን በነበረዉ የርስትና ጉልት የመሬት ስሪት በሰፈነበት በአፄዉ ሥርዓተ ስር በነበረዉ በአብዛኛዉ የወሎ ጠቅላይ ግዛት ሥር ነበር፡፡ የወሎ ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማም ደሴ ነበረች፡፡ በዚሁ ዘመን አርጡማ ፉርሲ አከባቢዎች በአፄዎቹ/በነገስታቱ ወይም በነገስታቱ ባለሟሎች በሚሾሙ ወረዳ ገዥዎች/አስተዳዳሪዎች ይገዙ ወይም ይተዳደሩ ነበር፡፡
የአፄዉ ሥርዓት በመገልበጥ አገሪቱን ወደ ሶሻሊስት ሥርዓተ ማህበር ለማሸጋገር የደርግ መንግስት ደፋ ቀና ሲል ከበርካታ ቡድኖች ሰፊ ተቃዉሞ ገጥሞት አገሪቱ ትርምስ ዉስጥ በነበረችበት ጊዜም በአብዛኛዉ አርጡማ ፉርሲና አከባቢዉ በወሎ ክፍለ ሀገር ስር ወረዳ አስተዳደር ሆኖ ሲተዳደር ቆይቷል፡፡ በኋላም ክፍለ ሀገሮች እንደገና ተከፋፍለዉ ሲደራጁ የወሎ ክፍለ ሀገር ደቡብ ወሎና ሰሜን ወሎ አስተዳደር አካባቢዎች ተብለዉ ሲዋቀሩ የአርጡማ ፉርሲና አካባቢዉ ህዝብ በደቡብ ወሎ አስተዳደር አካባቢ በተለያዩ ወረዳዎች ተጠቃሎ ሲተዳደር ኖሯል፡፡ በዚሁ የደርግ አገዛዝ ሥርዓት በአደረጃጀት ምንአልባትም በስም ለዉጥ ወረዳዎች አዉራጃ አስተዳደር/ግዛት ሲሆኑ ይህ ህዝብ የሚገኝበት ወረዳም የአዉራጃ አስተዳደርነት ስም ተሰጥቶት ነበር፡፡
ደርግ በኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሜክራሲያዊ ግንባር/ኢህአዴግ/ ከተተካ ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም በኋላም ኢህአዴግ ስልጣኑን እያጠናከረ መጥቶ ክፍለ ሀገሮችን በአዲስ መልክ ሲያደራጅና አዳዲስ ስሞች ሲሰይም የተለያዩ ክፍለ ሀገሮች ተዋህደዉ ክልል ሲቋቋም በመጀመሪያ የክልላችን መጠሪያ ክልል 3 ነበር፡፡ በኃላም የክልሉ መጠሪያ ስያሜ አማራ ክልል ሆኖ አስተዳደር አካባቢ ይባሉ የነበሩት የአስተዳደር እርከኖች የስም ለዉጥ በማድረግና አንዳንድ የተለዬ ቋንቋ፣ ዝርያ በአጠቃላይ የተለዬ ባህል ያላቸዉ ብሄረሰቦች ራሳቸዉን እንዲችሉ ተደርጎ ተመሠረተ፡፡ የተፈጠሩት የአስተዳደር እርከኖችም ዞን አስተዳደር/መስተዳድር ወይም አስተዳደር/መስተዳድር ዞን ተብለዉ ተሰይመዋል፡፡ በዚህም መሠረት ቀደም ሲል በአብዛኛዉ የሰሜን እና የደቡብ ወሎ አስተዳደር አከባቢዎች ይወከሉበት የነበረዉ የወሎ ክፍለ ሀገር በአራት ተከፋፍሎ በዋግኽምራ፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች ሲከፋፈል በ1986 ዓ.ም በአብዛኛዉ የኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪ የአከባቢዉን ህዝቦች በመጠቃለል የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን የተለያዩ ወረዳዎችን ይዞ ራሱን እንደ ዞን ሊዋቀር በቅቷል፡፡
በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ዉስጥ ከተዋቀሩ ወረዳዎች መካከል አንዱ አርጡማ ፉርሲ ወረዳ ሲሆን ይህ ወረዳ እንደ ወረዳ ሲቋቋም የወረዳዉ ዋና ከተማ ጭረቲ ነበረች፡፡ ወደ ኋላ አካባቢዉ የነበሩ ሌሎች ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦች ወደ አርጡማ ፊርሲ ወረዳ በመቀላቀላቸዉ የወረዳዉ ዋና ከተማ ከጭረቲ ወደ ጨፋ-ሮቢት ተዛወረ፡፡ ወረዳዉ ይህን ስም ከመያዙ በፊት ከጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ጋር ተቀላቅሎ ይተዳደር ስለነበር ስሙ አርጡማ-ጅሌ ወረዳ ነበር፡፡ ሆኖም የወረዳዉ የቆዳ ስፋትና የህዝብ ብዛቱ ለአስተዳደር አመች ባለመሆኑ በብሄረሰብ ዞኑ ምክር ቤት በ1994 ዓ.ም ወረዳዉ አርጡማ ፉርሲና ጅሌ ጥሙጋ በሚባሉ ወረዳዎች ለሁለት እንዲከፈል ሲወሰን የአርጡማ ፉርሲ ወረዳ አንዱ ወረዳ ሆኖ ዋና ከተማዉን ጨፋ-ሮቢት በማድረግ ለመቋቋም ችሏል፡፡ የአርጡማ ፉርሲ ወረዳ ባሁኑ ጊዜ ህዝቡን በ27 ቀበሌዎች አደራጅቶ ያስተዳድራል፡፡
የወረዳዉ አሰያየም ከሁለት ቃላቶች የተሰየመ ሲሆን አርጡማ የሚለዉ ቃል “አርጡሜ” ከሚለዉ ቃል የተሰየመ ሲሆን “አርጡሜ” ማለት በጣም ታዋቂና ቀደም ብሎ በአከባቢዉ አርፎ የሚኖር ግለሰብ ሲሆን አከባቢዉንም ሲያስተዳድር የነበረ ግለሰብ እንደሆነ ታሪክ ይናገራል፡፡ በአሁኑ ወቀትም አከባቢዉ አርጡማ በሚል ስም ይጠራል፡፡ ፉርሲ የሚለዉ ቃል “ፉርሴ” ከሚለዉ ቃል የተሰየመ ሲሆን “ፉርሴ” ማለት በጣም ታዋቂና አከባቢዉን ሲያስተዳድር የነበረ ግለሰብ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አከባቢዉ ፉርሲ በሚል ተሰይሞ ይጠራል፡፡ ስለዚህ የወረዳዉ ስም ከአርጡማ እና ፉርሲ የተሰየመ በዚህ በሁለቱ አከባቢዎች ባብዘኛዉን የወረዳዉ ህዝቦች የሚኖሩበትና በጣም ታዋቂ አከባዎች በመሆናቸዉ አርጡማ ፉርሲ በሚል ተሰይሟል፡፡
የጨፋሮቢት ከተማ አጠቃላይ መልክዓ ምድራዊ ሁኔታ፣
የጨፋሮቢት ከተማ በአርጡማ ፉርሲ ወረዳ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ከክልል ርዕሰ ከተማ ባህርዳር በስተደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ 580 ኪ/ሜ ርቀት፣ ከዞኑ ዋና ከተማ ከሚሴ በስተደቡብ አቅጣጫ 25 ኪ/ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ ከተማዋ በምስራቅ አማራ የልማት ቀጠና ዉስጥ የምትገኝ ሲሆን በገጠር ቀበሌዎች ተከባ የተካለለት ናት፡፡ ይህ ከተማ ህብረተሰቡን በአንድ የከተማ ቀበሌ አስተዳደር አዋቅራ በማስተዳደር ላይ ናት፡፡ የወረዳዉ ዋና ከተማ እንደመሆኗም የከተማነት ደረጃዋ በመሪ ማዘጋጃ ቤት ነዉ፡፡ የጨፋሮቢት ከተማ ከአምስት አመታት በፊት ጎልቶ የሚታየዉ ሚናዋ የመኖሪያነት ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን የንግድ እንቅስቃሴዎችና ወደ ኢንዱስትሪ ከተማነት ለመሸጋገር እየተጣጣረች ትገኛለች፡፡
የጨፋሮቢት ከተማ ታሪካዊ አመሠራረትና የስም ስያሜ፣
በአሁኑ የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን በሚገኘዉ አርጡማ ፉርሲ ወረዳ የጨፋሮቢት ከተማ ከመመስረቷ በፊት አከባቢዉ በዘዉዳዊ አገዛዝ፣ በርስትና ጉልት የመሬት ስሪት ሥረዓት ይተዳደር ነበር፡፡ በንጉሳዊዉ አገዛዝ አጥቢያም ዳኛ ሲመራ ቆይቷል፡፡ በዚህ ጊዜ ከተማዋ የተመሠረተችበት አከባቢ ጫካ የነበረና ከፍ ባሉ ቦታዎች ላይ በግብርና ይተዳደር የነበሩ ሰዎች አልፎ አልፎ ከመኖራቸዉ በስተቀር ብዙ ሰዉ ያልሰፈረበት ነበር፡፡ በአሁኗ ጨፋሮቢት ከተማ ያለችበት ቦታ መጀመሪያ የሰፈሩት ኢትዮጵያ ኢጣሊያ ተወራ ጥቂት ጊዜ (5 ዓመት ገደማ) ከቆየች በኋላ በኢትዮጵያ አርበኞች ያልተቋረጠ ትግል ኢጣሊያ ተሸንፋ ስትወጣ አፄ ኃይለስላሴ ከእንግሊዝ አገር ስደት በኋላ ወደ አገራቸዉ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ኢትዮጵያን ለመርዳት በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ኢትዮጵያ የገቡ አፍሪካዉያን የእንግሊዝ ወታደሮች ነበሩ፡፡ ከእንግሊዝ ወታደሮች መካከል የሱዳን ዜጎች ይገኙበት ነበር፡፡ ኢጣሊያዉያን ተጠራርገዉ ሲወጡና በኢትዮጵያ መረጋጋት ሲመጣ እነዚህ የሱዳን ዜጎች በሰሜን ኢትዮጵያ ሲንቀሳቀሱ አንዳንድ አነስተኛ ወታደራዊ ቡድኖች በየደረሱበት መስፈር ጀመሩ፡፡ ሱዳኖች ከሰፈሩባቸዉ አከባቢዎች የአማራ ክልል ምስራቃዊ ክፍል አንዱ ነበር፡፡ በመሆኑም ከእነዚህ ሱዳኖች መካከል የተወሰኑት በአከባቢዉ የነበረን ዓሳ በመጠቀምና እንጨት በማክሰልና በመሸጥ ጨፋሮቢት አከባቢ በመስፈር ተቀመጡ፡፡ ከእነዚህ የሱዳን ዜግነት ያላቸዉ ሰዎች መካከል ሳሊምና አብደላ የሚባሉ ይገኙበት ነበር፡፡ በዚህ አከባቢ ከሱዳኖች ሌላም ከጎጃም የመጡ ይማም አደራ፣ ከትግራይ የመጡ አባ ንጉሴ እንዲሁም ከሴት ጣይቱ ጎሼ የሚባሉም ሰዎች ይኖሩ ነበር፡፡ እነዚህ ሱዳናዉያንና ከጎጃምና ከትግራይ የመጡ ኢትዮጵያዉያን ለከተማዋ መቆርቆርና ወደ አከባቢዉ ሰዎች እንዲሰባሰቡ የራሳቸዉ አስተዋፅኦ ነበራቸዉ ማለት ነዉ፡፡ በዚህ አከባቢ እንዲሰፍሩ ያደረጓቸዉ ምክንያቶች በአከባቢዉ ዓሳ ከመኖሩ በተጨማሪ ለመኖሪያና ለግብርና ሥራ ምቹ መሆኑና አከባቢዉ ልምላሜና ዉኃ እንዲሁም ደን ያለዉ መሆኑ ነበር፡፡ ከተማዋ በመጀመሪያ የተቆረቆረችዉ በደቡብ ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አከባቢ ሲሆን ቀስበቀስ ወደ ሰሜን እያደገች መጣች፡፡ ከሱዳኖች መምጣት በፊት አከባቢዉ ከመንገድ በላይ(ወደ ዳገቱ) ወሎ ከመንገድ በታች(ወደ ሸዋ አቅጣጫ) ሸዋ ተብሎ የተከፋፈለ ነበር፡፡ ወሎ ጥፋት አጥፍቶ ወደ ሸዋ የገባ ሰዉ በሸዋ በኩል ካልሆነ በስተቀር በጥፋቱ የወሎ ወገን ተሻግሮ መያዝ የማይቻል እንደነበረ የአከባቢዉ ሽማግሎዎች ይገልፃሉ፡፡ ጨፋሮቢት ከመባሉ በፊት አከባቢዉ ጨፋ-ድሬ ይባል እንደነበር፣ ጨፋ-ድሬ ማለት ዉሃማ አከባቢ ማለት እንደሆነና የአሁኑ የከተማዋ ስያሜ በግምት ከ1934 ዓ.ም አከባቢ ጀምሮ ጨፋሮቢት እንደተባለ የከተማዋ ታዋቂ ግለሰቦችና ሽማግሌዎች ያስረዳሉ፡፡ ቀደም ሲል በአከባቢዉ ጨፋ-ድሬ የሚባል ገበያ የነበረ ሲሆን በተለያዩ ጊዜ ወደ ተለያዩ አከባቢዎች ተዛዉሯል፡፡ በኃላም ረቡዕ ቀን የሚዉል ረቡዕ ገበያ ተቋቋመ፡፡ ጨፋሮቢት የሚለዉ የዛሬዉ የከተማዋ ስምም የተወሰደዉ ከዚሁ የገበያ ስም ነዉ፡፡
በ1953 ዓ.ም አሁን ጨፋሮቢት ካለችበት አለፍ ብሎ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶ ስለነበር ለተጎጂዉ ህዝብ እርዳታ ለመስጠት የእርዳታ እህልም ሆነ ሌሎች ቁሳቁሶች ማከማቻና ማከፋፈያ ሆና የነበረችዉ ጨፋ-ሮቢት ስለነበረች ይህ ሁኔታ የበለጠ ህዝብ እንዲሰባሰብበትና የከተማነት መልክ እንድትይዝ አድርጓታል፡፡ ቀስበቀስም የምግብና መጠጥ ቤቶች በተለይ ከምግብ በተጨማሪ መሪሳ የሚባል መጠጥ አገልግሎቶች በመጀመራቸዉ ከተማዋ እየደመቀችና እየሞቀች መጥታለች፡፡
የጨፋሮቢት ከተማ ተመስርታ እያደገች ስትመጣ የተለያዩ የሰፈር ስሞች የተሰየሙ ሲሆን የመጀመሪያዉ የሰፈር ስም አረገም ይባላል፡፡ ቀጥሎም ሟጣ፣ ጉለልሻ፣ ብሔ ወደያ፣ ቀራሩ፣ መንጉዶና ቡየና የሚባሉ ሰፈሮች ተፈጥረዋል፡፡ ጨፋሮቢት በንጉሱ ዘመን በ1954 ዓ.ም መቶ አለቃ ጎንፋ በዳሶ በተባለ ግለሰብ ከተተከለ ወፍጮ ቤት አገልግሎት አገኘች፡፡ በ1961 ዓ.ም የ1ኛ ደረጃ ት/ቤት ተጠቃሚ ሆናለች፡፡ በአፄዉ ሥረዓት መገባደጃና በደርግ ሥረዓት መጀመሪያ ላይ በ1967 ዓ.ም ደግሞ የከተማዋ ከጥልቅ ጉድጓድ ንፁህ ዉኃ ማግኘት ችላለች፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ(ኢህአዴግ) ስልጣን ከያዘ በኃላም በ993 ዓ.ም ለከተማዋ የተከማ እድገት ፕላን ተዘጋጀላት፡፡ በ997 ዓ.ም ማዘጋጃ ቤት ተቋቋመላት፡፡ በ1998 ዓ.ም የዲጂታል ስልከ ተጠቃሚ እንዲሁም በ1999 ዓ.ም ደግሞ የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት አገኘች፡፡ በአሁኑ ጊዜም በከተማዋ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬና አርጎባ ብሄረሰቦች የሚኖሩ ሲሆን ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ(አንድ 1-8ና አንድ ከ1-4)፣ አንድ ሁለተኛ ደረጃ(9-10)፣ አንድ መሰናዶ(11-12) ትምህርት ቤቶቸ፣ አንድ ጤና ጣቢያና አንድ የእንስሳት ጤና ክሊኒክ አገልግሎት እንዲሁም አንድ ቴ/ሙያ ት/ስልጠና ኮሌጅ ያለባት ከተማ ናት፡፡ በቀጣይ አመታት ደግሞ አንደ ሆስፒታል ግንባታ ለመገንባት እደል አግኝታ መሠረተ ደንጋይ ተቀምጦለታል፡፡
የወረዳዉ ዋና ከተማ አሰያየም
የወረዳዉ ዋና ከተማ ጨፋ ሮቢት የተባለ አሰያየም ያለዉ ሲሆን አሰያየሙም ከሁለት ጥምር ቃላቶች በመነሳት የተሰየመ ነዉ፡፡ “ጨፋ” ማለት አከባቢዉ ጨፋማ ዉሃ አዘል አከባቢ በመሆኑ እርጥብ ማለት ሲሆን በጨፋ የተሰየመ ሲሆን “ሮቢት” ማለት የአከባቢዉ የገበያ ቀን እሮብ እለት በመሆኑ ከዚህ በመነሳት “ሮቢት፤ በሚል የተሰየመ ሲሆን ከዚህ በመነሳት የወረዳዉ ዋና ከተማዋም “ጨፋ ሮቢት” በሚል ስያሜ ተጠራች፡፡
የወረዳዉ ታሪካዊ ቦታዎችና መስህቦች፣
ቅርሶች ቁሳዊ ባህልና መንፈሳዊ በማለት ለሁለት ይከፈላሉ፡፡ ቅርሶች ለህብረተሰቡ የዉበት፣ እድገት፣ የማንነት ወዘተ መገለጫዎች እንዲሁም የጥንት ስልጣኔ፣ የረጅም ጊዜ ታሪክና መልካም የተፈጥሮ ገፀታዎችን የሚያሳዩ ናቸዉ፡፡ ቅርስ በቅድመ ታሪክ ዘመንና በታሪክ ዘመን ሰዉ ልጅ የፈጠራና የስራ እንቅስቃሴ ዉጤት የሆነ የተፈጥሮ፣ የለዉጥና ሂደትን የሚገልፅና ሚመሰክር በሳይንስ፣ በታሪክና፣ በባህል፣ በስነ ጥበብና እደ ጥበብ ይዘቱን ከፍተኛ ተፈላጊነትና ዋጋ ያለዉ ማንኛቸዉም ግዙፍነት ያለዉና የሌለዉ ነገር ነዉ፡፡ እንዲሁም የአንድ ሀገር የማንት መገለጫ፣ የታሪክ፣ የባህል፣ የወግ ልማድ ስረዓትን የሚያሳይ ካለፈዉ ትዉልድ የተወረሰና ለመጪዉ ትዉልድ የሚተላለፍ የብዙ ዘመናት የስራና የፈጠራ ዉጤት ነዉ፡፡ ቅርሶች ለትዉልድ ከመተላለፋቸዉም ባሻገር ለሀገር ገፅታ ግንባታ እንዲሁም የቱሪዝም ልማትን ከማሳደግ አንፃር ጠቀሜታቸዉ የላቀ ነዉ፡፡ ከጠቀሜታቸዉ በጥቂቱ ፡፡ ቅርሶች የአንድ ህዝብ የዘመናት የኑሮ እንቅስቃሴ፣ የስራና የፈጠራ ክንዉን መዘክር ሲሆኑ የሰዉ ልጅ የተጓዘባቸዉን የለዉጥና የእድገት ሂደት እንዲሁም ተፈጥሮና አካባቢን ይበልጥ ለመረዳት ለሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች ምትክ የሌላቸዉ የመረጃ ምንጮች በመሆን ያገለግላሉ፡፡ የሰዉ ልጅ የሳይንስና እደ ጥበብ ዕደገትን ጥናትና ምርምር ለማድረግ መነሻ በመሆን ያገለግላሉ፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገትን በማፋጠንና በስልጣኔ ወደ ፊት ለመራመድ መሠረት በመሆን ጥቅም ይሰጣሉ፡: ቅርሶች አንድ ሀገር ህዝብ የሀገሩን ታሪክና ባህል በበለጠ አንዲያዉቅና እንዲማር ከመርዳታዉም በላይ ሀገራዊ ስሜንትና ፍቅርን በማጎልበት እንድነትን በማጠናከር የሀገርና ህዝብ መለያ በመሆን ያገለግላሉ፡፡ ከማንነት መገለጫ በተጨማሪ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠሜታ አላቸዉ፡፡
ቱሪዝም በአለም ላይ ፈጣን ዕድገት እያመጡ ካሉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች አንዱ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት አገራዊ ልማትን በመደገፍና በማፋጠን ረገድ የበኩሉን አስተዋፆ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ቱሪዝም በዉጭ ምንዛሬ ምንጭነት ጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ የምርትና አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን በማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋፆ ያበረክታል፡፡ ቱሪዝም በባህሪዉ የሰዉ ጉልበት በሰፋት የሚጠቀም በመሆኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ለወጣቶችና፣ ለሴቶችና አካለ ጉዳተኞች የስራ እድል መፍጠር ይችላል፡፡
ቱሪስት ማለት አንድ ግለሰብ ወይም ሰዉ ከሚኖርበት ቦታ በተለያየ ምክንያት ለ24 ሰዓት ቢሄድ እዛ ላረፈበት ሀገር ወይም ስፍራ እርሱ ቱሪስት ነዉ፡፡ በአለማችን የቱሪስት መስህብ ያላቸዉ ሀገሮች በርካታ ሲሆኑ እነዚህ አገሮች ቱሪስቶችን እንደ አንድ የኢኮኖሚ ምንጭ ይጠቀሙባቸዋል፡፡ የአገራችን ኢትዮጵያም በርካት የመስህብ ሀብቶች ካላቸዉ አገሮች ትመደባለች፡፡ በወረዳችን ያለዉን የመስህብ ሀብት በማልማት፣ በማስፋፋትና ለቱሪዝም አገልግሎት በማብቃት የወረዳችንን ሁለንተናዊ ዕድገት ልናፋጥን ይገባል፡፡
ወረዳው የብዙ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች መገኛ /ባለቤት/ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል የሼህ ኡመር መካና መቃብር፣ የቆንቦሮ ጥንታዊ አረቦች መቃብር፣ የደሬንሳ ዋሻ ፣ የሁሶ ጥንታዊ መስጊድ እና የአሸዋ ሉጤ ፍል ዉሃ ይገኙበታል፡፡ በወረዳዉ የተለያዩ ታሪካዊ ቦታዎችና መስህቦች ያሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ተጠንተዉ በወረዳዉ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት በታሪክነት የተመዘገቡ ቦታዎች እንደሚከተለዉ ቀርበዋል፡፡
ተ.ቁ
|
የመስህቡ ስም
|
የሚገኝበት ቦታ
|
ዞን
|
ወረዳ
|
ቀበሌ
|
ጎጥ
|
ልዩ ቦታ
|
የአሰራር ሁኔታ
|
ከወረዳዉ ያለዉ ርቀት
|
01
|
ቆምቦሮ የአረቦች ቀብር
|
ኦሮሞ
|
አርጡማ ፉርሲ
|
ጌሎ
|
ፈቴ
|
ቆምቦሮ
|
ሰዉ ሰራሽ
|
20 ኪ.ሜ
|
02
|
ሁሶ ቀብር
|
ኦሮሞ
|
አርጡማ ፉርሲ
|
ቂጭጮ
|
ሁሶ
|
ሁሶ
|
ሰዉ ሰራሽ
|
22 ኪ.ሜ
|
03
|
አሸዋ ሉጤ ፍል ዉሃ
|
ኦሮሞ
|
አርጡማ ፉርሲ
|
አሸዋ ሉጤ
|
ሉጤ
|
-
|
ተፈጥሯዊ
|
7 ኪ.ሜ
|
04
|
ሸህ ኡመር ቀብር
|
ኦሮሞ
|
አርጡማ ፉርሲ
|
ጎልቦ አርባ
|
ሸህ ኡመር
|
ዋልኬ
|
ሰዉ ሰራሽ
|
10 ኪ.ሜ
|
05
|
ደሬንሳ ዋሻ/ጉርጓድ
|
ኦሮሞ
|
አርጡማ ፉርሲ
|
ደሬንሳ
|
ኡሉ
|
-
|
ተፈጥሯዊ
|
|
06
|
ጄኔራል አበበ ገመዳ ግምብ
|
ኦሮሞ
|
አርጡማ ፉርሲ
|
ቂጭጮ
|
|
|
ሰዉ ሰራሽ
|
2 ኪ.ሜ
|
07
|
አንገል ድልድይ
|
ኦሮሞ
|
አርጡማ ፉርሲ
|
ቂጭጮ
|
|
|
ሰዉ ሰራሽ
|
22 ኪ.ሜ
|
1. የቆምቦሮ የአረቦች ቀብር
የቆምቦሮ አረቦች ቀብር ከወረዳዉ ዋና ከተማ ጨፋሮቢት በ20 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በጌሎ ቀበሌ የሚገኝ ታሪካዊ ቦታ ነዉ፡፡ ቦታዉ የአየር ሁኔታዉ ሞቃታማና በረሃማ አከባቢ ሲሆን በከፍታ ቦታ ላይ የሚገኝና በደን ተከቦ ይገኛል፡፡ የቆምቦሮ መካነ መቃብር ቦታ በአርጡማ ፉርሲ ወረዳ ጌሎ ቀበሌ ልዩ ስሙ ቆምቦሮ በሚባለው ቦታ የሚገኝ ነው፡፡
የመቃብር ቦታው መቼ እንደተጀመረ ትክክለኛ ማስረጃ ባይገኝም 13ኛ ትውልድ ደርሰናል የሚሉ የአካባቢው አዛውንቶች ከ1000 ዓመት በላይ ይሆነዋል ይላሉ፡፡ መቃብሩ የማን እንደሆነ በአዛውንቶች የሚጠቀሰው በመቃብሩ ድንጋዮች ላይ በአረብኛ ቋንቋ ተጽፎ የነበረ ጽሁፍ ሙሉ በሙሉ ይነበብ በነበረበት ወቅት በሁለተኛ ሂጅራ ወደ ኢትዮጲያ የመጡ አረቦች መቃብር መሆኑን፣ የተቀበሩ ሰዎች ብዛት 44 እንደሆኑና 2 ሴቶች መሆናቸውንና ለይፋት መንግስት መልዕክት አድርሰው ሲመለሱ ባጋጠማቸው ውጊያ እንደሞቱ ይገለፃል፡፡ ይህ ሊረጋገጥ የሚችለው በጽሁፎቹ ላይ አርኪዎሎጅካል ጥናት ሲደረግ ብቻ ነው፡፡
በሌላ ወገን ደግሞ በቅርብ ጊዜ አንዳንድ የእድሜ ባለፀጋ ሽማግሌዎች እንደሚሉት ከሆነ ይህ ቀብር ቦታ የተገኘዉ በህልም ምክንያት ነዉ ይላሉ፡፡ የአገር ሽማግሌዎቹ እንደሚሉት የዚህ ቀብር ቦታ ግኘት ምክንያት ወልይ ዘይዱ የሚባለዉ በህልም እንዳገኘዉ ይጠቁማሉ፡፡ ወልይ ዘይዱ መኖሪያ ቤቱ አጣዬ ከተማ አከባቢ ሲሆን በህልም ካዩ በኋላ ወደ ቀብር ቦታዉ ቆምቦሮ በመሄድ በዚያን ወቅት አስተዳዳሪ ከነበሩት ቀኝ አዝማች አልይ አደሜ ጋር ተገናኝተዉ ስለ ቀብሩ በሰፊዉ ዉይይት ካደረጉ በኋላ የቀብሩ ቦታዉን ህዝብን በማስተባበር ለጥናት እንዲቆፈር አድርገዉ እንዲጠና አደረጉ፡፡ ህዝቡም ቀብሩ ለምን ተቆፈረ የሚለዉ ጥያቄ ዉዝግብ ፈጠረባቸዉ፡፡ ይሁን እንጅ ጥያቄዉን ለወልይ ዘይዱ አላቀረቡም፡፡
.
ቀብሩም ከተቆፈረ በኋላ በቀብሩ ዉስጥ ካለዉ ድንጋይ ላይ ቀብሩ የአቦች መሆኑን፣የተቀበሩ ሰሃባዎች ስም ዝርዝር እና ከየት ቦታ እንደመጡ የሚገልፅ የጽሑፍ መረጃ ማግኘት ችለዋል ይላሉ፡፡ በተጨማሪም ሰሃባዎቹም ከሳኡዲ አረቢያ፣ ከየመን፣ ከሶሪያ፣ከኢራቅ እና ከኩዌት አገሮች የመጡ አረቦች መሆኑን የሚገልፅ መረጃ እንዳገኙ ይናገራሉ፡፡ በዚህ ቀብር የተቀበሩ ሰዎች ብዛትም 44 እንደሆኑና ከእነዚህ ዉስጥም 2 ሴቶች እንደሆኑ ድንጋዩ ላይ ከተፃፈዉ መረጃ ለማግኘት ችለዋል ይላሉ የአገር ሽማግሌዎቹ፡፡ እነዚህ ሰሃባዎች ወደ ኢትዬጵያ የመጡበት አላማቸዉም የእስልምና ሃይማኖትን ለማስፋፋትና ዳዕዋ ለማድረግ እንደሆነም ይጠቁማሉ፡፡ ስማቸዉም በዝርዝር ሲገለፅ ኢስማኢል ጀበርቲ፣ አብደላ ኢብኑ ማሊክ፣ ቃሲም አብዱረህማን እና ኢብኑ አፉን እንደሆኑም በድንጋዩ ላይ ከተፃፈዉ ጥቂት መረጃ ለማግኘት እንደቻሉም ይገልፃሉ፡፡ በቅርብም ጊዜም አንድ ከአረብ አገር ሰዉ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በካርታ ተከታትሎ መጥቶ ጎብኝቶ እንደሄደም የአገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡
2. የሼህ ኡመር መካነ መቃብር
የሸህ ኡመር መካነ መቃብር ከወረዳዉ ዋና ከተማ ጨፋ ሮቢት 12 ኪ.ሜ ርቀትላይ ይገኛል፡፡ የሼህ ኡመር መካነ መቃብር ከሌሎች ለየት ያለ የመሰህብ ሀብት ነው፡፡ ይህም በየ አመቱ በመቃብሩ ስፍራ በአራት ቀናቶች የተከፈለ ክብረ በዓልን ያስተናግዳል፡፡
የሼህ ኡመር መካነ መቃብር ሰፍራ ከወረዳው ካሉት መስህብ ሀብቶች አንዱ ነው፡፡ መካነ መቃብሩም ከፍ ያለ ቦታ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም ስፍራ በየዓመቱ ዚያራ ይዘጋጃል፡፡ እንዲሁም በዕለቱ የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡ እለቱም ማክበርና መዘከር የተጀመረበት ቀን በውል ባይታወቅም 160 ዓ.ም ማስቆጠሩን የአከባቢ አዘውንቶች ይናገራሉ፡፡ በዚህም ቦታ በየዓመቱ በአንድነት ተሰባስበው የሚዘክሩበት ምክንያት የሼህ ኡመርን ታሪክ፣ እለተ እረፍትና የድል ቀን ሳይረሳ ለትውልድ ለማስተላለፍ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ሰዎች በተለያዩ ጊዜ ቦታ የአንድን ክዋኔ ስረዓት በተደጋጋሚ ሲከዉኑት ይታያል፡፡ ይህ ተከታታይና ድግግሞሽ በህብረተሰቡ ውስጥ ልማድን እንዲሁም ባህልን የአንድነት፣ የመቻቻልና የመተሳሰብ ትስስርን ይፈጥራል፡፡ የሰው ልጅ የጀመረውን ክዋኔ /ክብረ በዓል ወዘተ/ ለማዝለቅ እንደየ አከባቢው ቋንቋ፣ አኗኗርና ክስትት የተለያየ ይሁን እንጂ የራሱ የሆነ መነሻ ሀሳብ ወይም ድርጊት አለው፡፡ በአጠቃላይ ምክንያቱም መነሻ ሊኖረው ግድ ነው፡፡ ስለሆነም ሸህ ኡመር መካነ መቃብር ስፍራ የሚከወነው ክዋኔም ከዚህ እንድምታ የዘለለ አይሆንም፡፡
ሼህ ኡመር መቼ እንደተወለዱ በወል ባይታወቅም ከኦሮሚያ ክልል ከአርሲ እንደመጡ ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ ከመላ ምት የዘለለ የጽሁፍ ማስረጃ የለም፡፡ ሼህ ኡመር ከትውልድ ስፍራቸው አርሲ ለመውጣትና አርጡማ ለመምጣት ያነሳሳቸው አንድ ምክንያት ነበር፡፡ ይህም እስልምና ሀይማኖትን ማስፋፋት ወይም ሀይማኖቱ ባልተዳረሰበት ቦታ ሁሉ ማዳረስ ነው፡፡ እንደመጡም ኡታልቴ በተባለ መንደር ነበር ያረፉት፡፡ በኋላም ጂሃድ /ሀይማኖታዊ ጦርነት/ አካሄዱ፡፡ በዚህም ጦርነት ክርስትና የተባለ ሀይማኖትን አጥፍቶ እስልምና እንዲስፋፋ ማድረግ ሲሆን የሼህ ኡመር ጦር ገፍቶ በስፋት ሲገባ በወቅቱ ገዢ የነበረው ሹም ሽሽት ገባ በጦርነትም ድልን በማግኘት ሀይማኖቱን ማስፋፋት ችለዋል፡፡
በመካነ መቃብሩ ላይ ክብረ በዓልን ማክበር የዛሬ ጅማሬ ባይሆንም የራሱ የሆነ መነሻ ሀሳብ አለው፡፡ ይሄም ሼህ ኡመር ሀይማኖታዊ ጦርነት /ጅሃድ ከማወጅ ባሻገር ተዓምር የሚያሰኝ ገድል መፈፀማቸው ነው፡፡ እንዲሁም ሀይማኖታዊ ሰውና ለሀይማኖቱ የተጋደሉ ሀይማኖታዊ ጀገግና መሆናቸው እንደሆነ የእካባቢው ህብረተሰብ ይናገራል፡፡
ሼክ ኡመር ፈጽመዋል ከሚባሉት ገድል መካከል አንዱ ጅሃድ ማወጅ ሲሆን ሌላኛው በሙስበሃ የሰሩት ተዓምር ነው፡፡ ይህም ተዓምር አርጡሜ በተባለው ገዢ ላይ የተፈፀመ ነው፡፡ አርጡሜ በወቅቱ ይገዙ ከነበሩት ሹሞች ውስጥ አንዱ ቢሆንም አምባገነን መሪ ነበር፡፡ በአብዛኛው ባህሉ ውስጥ በሰርግ የተጋቡ ጥንዶች ተሞሸረው ሚስት ወደ ባል ቤት መሄድ ስርዓቱ ነው፡፡ ነገር ግን በወቅቱ በአከባቢው ይከሰት የነበረው ከዚህ ማህበራዊ ልምድ፣ ኩነት፣ ባህል ለየት ያለ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰርግ ተሰርጎ ሙሽራዋ ከቤተሰቧ ተለይታ ወደ ባል ቤት በመሄድ ፈንታ አርጡሜ ወደ ተባለው ገዢ ቤት ተገዳ ትወሰዳለች፡፡ በመሆኑም ሚስት ወደ ባል ከመሄዷ በፊት ከእርሱ ጋር አንሶላ መጋፈፍ ግድ ነበር ፡፡ ጥንዶቹ እለቱን በደስታ ላይሆን በሃዘን ነበር የሚያሳልፋት፡፡ አበው ‹‹ የለመደች ጦጣ …….››› እንደሚሉት ሁሉ ይህ ሰው የሁል ጊዜ ተግባሩ ነውና የሼህ ኡመር ሚስት በእይታው ውስጥ ገባች፡፡ ሹም ሚስቱን እንዲያቀርብ መልዕክኛ ወደ ሸህ ኡመር ላከበት፡፡ ሼህ ኡመር በሰርጋቸው እለት ይህ ተግባር እንደሚፈፀም ያውቁ ነበርና ሚስታቸውን በነፃነት ወደ እርሱ ሸኟት፡፡ በዚህ ጊዜ ሙስበሃ ለሚስታቸው ሰጥተው ምን ማድረግ እንደለባት አስረድተው ላኳት፡፡ እርሷም ፊቱ ስትደርስ በተባለችው መሠረት ሙስበሃውን ወደ አርጡሜ ወረወረች፣ ወዲያው እባብ ሆኖ ተቀየረና እባቡም ሹሙን ከእግር እስከ አናቱ ተጠምጥሞ ገደለው፡፡
በአጠቃላይ በሼህ ኡመር መካነ መቃብር ላይ የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡ በመሆኑም በዚህ ዚያራ ላይ የሚከናወኑ ክዋኔዎችም ሆኑ ጅማሬው ገድላቸውን፣ ታሪክና አስተምህሮታቸውን ለማስታወስ እንዲሁም ለመዘከር ነው፡፡
3. የጄኔራል አበበ ገመዳ ግምብ
የጄኔራል አበበ ገመዳ ግምብ ብዙ አመታትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ግምብ ሲሆን በ1953 ዓ.ም የጦር መሪ አዛዥ በሆኑት በጄኔራል አበበ ገመዳ ከዉብ ድንጋይ የተሰራ ታሪካዊ ግምብ ነዉ፡፡ ግምቡ ብዙ አመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ከጠንካራና ዉብ በሆነ ድንጋይ የተሠራ በመሆኑ ባሁኑ ወቅትም አዲስ እንደተሠራ ግምብ የሚያምር ነዉ፡፡ ግምቡም የሚገኘዉ ከወረዳዉ ዋና ከተማ ጨፋሮቢት ወደ ምስራቅ አቅጣጫ በ21 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ቂጭጮ በሚባል ቀበሌ ዉስጥ ይገኛል፡፡
ግምቡ በ1952 ዓ.ም በሠራዊት መሪዉ ጄኔራል አበበ ገመዳ መሠረተ ድንጋይ አስቀመጠ፡፡ ቀጥሎም በ1953 የግምቡ ግንባታዉ ተጀምሮ ባጭር ጊዜ ዉስጥ ተጠናቀቀ፡፡ የግምቡ አሠራር በ--- ሄክታር ላይ የተሠራ ሲሆን በ6 ብሎኮች ተከፋፍሎ የተሠራ ግምብ ነዉ፡፡ እነዚህ እያንዳንዱ ብሎኮች የየራሳቸዉ የተሠራበት ዓላማ አላቸዉ፡፡
· 1ኛ ብሎክ ለባለ ስልጣኖች መኖሪያ ተብሎ የተሠራ ነዉ፡፡
· 2ኛ ብሎክ ለባለስልጣኖች ቢሮ ተብሎ የተሠራ ነዉ፡፡
· ሎሎቹ ብሎኮች ለልዩ ልዩ ሠራዊት አገልግሎት እንዲዉል ተብሎ የተሠሩ ናቸዉ፡፡
የግምቡ አሠራረር
ይህ ግምብ በጣም ዉብ ካደረጉት የአሠራሩ ሁኔታዎች በጣም የሚያስደስት ሲሆን የሚያብለጨልጩና የሚያምሩ ጥቁር ድንጋዮችን ማክ በሚባል መኪና ታግዞ በማቅረብ፣ በዉሃና አሸዋም ጃራ ከተባለ የተጋዘ ሲሆን ትላልቅና የሚያምሩ ኮርነር ላይ የሚሆኑ ድንጋዮች “ማሽሌ” ከሚባል” አከባቢ የተጋዘ ሲሆን እንደ ሲሚንቶ ለማቡኪያና ለማጠናከሪያ የሚሆን “ኖራ” የሚባል አፈርን “ሸህ ሙቅሪ” ከሚባል አከባቢ በህ/ሰቡና በአህያ ጉልበት ታግዞ የተሠራ ዉብ ግምብ ነዉ፡፡
ይህን ግምብ የሠሩት ግንበኞችና ሠራተኞች ደግሞ በዚያን ወቅት የአከባቢዉ ነዋሪዎች የሠለጠኑ ባለመሆኑ የቀን ስራ መስራት ስለማይፈልጉ ከደቡብ ወሎ ዞን ከዚያ በፊት ከጣሊያኖች ጋር የሚሠሩና ልምድ ያላቸዉን ባለሙያዎችና ሠራተኞች በማስመጣት በቀን አንድ አንድ ብር ተከፍሏቸዉ የሚሠሩ በሁለት መኪና ሠራጠኖች በማስመጣት ግምቡ በሚያምር መልኩ ተገንብቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለዚህ ግንባታ ቁሳቁስ የተጠቀሙበት የጣሊያን ቆርቆሮ፣ጣዉላ፣ ምስታወት፣ የጣዉላ በር፣ ሚስማር፣ ኮርኒስ፣ ወዘተ ከአዲስ አበባ በማስመጣት የተገነባ ግንብ ነዉ፡፡ ይህም ቆርቆሮዉ ክብደቱ 5ኪግ የሚመዝን ሆኖ የአንዱ ዋጋ 6 ብር ሲሆን ግንባታዉ የፈጀዉ ቆርቆሮ ብዛትም 2000 ነዉ፡፡ ጣዉላዉም ከዝግባ ዛፍ የተመረተ ነዉ፡፡ ባጠቃላይ የግንቡ ዉፍረት 60 ሳንቲ ሜትር ሲሆን ግንባታዉን ለማጠናቅም የወሰደባቸዉ ጊዜ አንድ አመት ከ ስድስት ወር ሲሆን አጠቃላይ የወሰደባቸዉ ካፒታልም 100,000 (አንድ መቶ ሺህ) ብር እንደ ሆነ በዚያን ጊዜ ከነሱ ጋር የነበሩት ባለሃብት አቶ ኡመር አበበ እና አቶ ሀሰን አብደሌ አብራርተዉታል፡፡
4. የአንገል ድልድይ
የአንገል ድልድይ ከቂጭጮ ቀበሌ 10 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከወረዳዉ ዋና ከተማ ጨፋሮቢት ደግሞ በ31 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ታሪካዊ የህዝብ መሸጋገሪያ ድልድይ ከ 1947 ዓ.ም በፊት ሁለት ጎረቤት ወረዳዎችን ለማገናኘት (አርጡማ እና ደዌ) ታስቦ ደዛችማች የሱፍ ብሩ በተባለ ግለሰብ ሁለቱን ህዝቦች ለማገናኘት ታስቦ በቦርከና ዉሃ ወንዝ ላይ ለመሸጋገሪያነት ተሠራ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሆኖ የአዉራጃ ሥራ አስኪያጁ ደዛችማች የሱፍ ብሩ ህዝቡን በማስተባበር በዛ አከባቢ በሚገኙ ጠንካራ እንጨቶችን በማስቀረብ ተሠርቶ አገልግሎት እየሰጠ እንዳለ ከ3 አመታት እድሜ በኋላ የቦርከና ወንዝ በከፍተኛ ደረጃ ሞልቶ ድልድዩን ሰበረዉ፡፡ ድልድዩ ከፈረሰ በኋላ የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት ስለተቋረጠ በዚህ መቀጠል የለበትም በማለት ህዝቡ ተወያይተዉ በ1947 ዓ.ም ሠላማዊ ሰልፍ በመዉጣት በወቅቱ ለነበረዉ ገዥ ለጄኔራል አበበ ገመዳ ድልድዩ ይሠራልን በማለት ጥያቄያቸዉን አቀረቡ፡፡ ጄኔራል አበበ ገመዳም ጥያቄያቸዉን በመቀበል ድልድዩ በሚገኝበት ቦታ በአካል በመቅረብ ካጠኑት በኋላ ምንም ጊዜ ሳይፈጅ እንዲሠራ በማድረግ የአርጡማና ደዌ ህዝቦች ግንኙነት እንዲቀጥል አደረጉ፡፡
የአንገል ድልድይ በሚያስደንቅ ሁኔታ አሠራሩ ከብረታብረትና ጣዉላን በመጠቀም የተሠራ ሲሆን ስፋቱም ------ ሜትር እና ርዝመቱም ----- ሜትር ነዉ፡፡ በዚህ ድልድይ ላይ ለብዙ አመታት ሰዎች፣ የቤት እንስሳቶች እንደ አህያ፣ ከብቶች፣ ወዘተ በመተላለፍ አገልግሎት ሲሰጥና ሲጠቀሙበት ቆይተዋል፡፡ የአንገል ድልድይ እስካሁን ድረስ ለ55 አመታት ሲያገለግል የቆየ ሲሆን በአሁ ወቅት በማርጀቱ ምክንያት ጥገና ሳይደረግለት ስለቆየ ክረምት ክረምት ብቻ የሰዎች መሸጋገሪያ ሆኖ እያገለገለ ነዉ፡፡
5. የደሬንሳ ዋሻ
የደሬንሳ ቀበሌ በወረዳዉ ዉስጥ ከሚገኙ ቀበሌዎች አንዷ ስትሆን ከወረዳዋ ዋና ከተማ ጨፋሮቢት በ18 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ደሬንሳ ከኦረምኛ ቃል የመጣ ሲሆን በአከባቢዉም በብዛት ደሬንሳ የሚባል ሳር ስለሚበቅልበት ቀበሌዋ ስያሜዋን ልታገኝ ችላለች፡፡
ይህ ዋሻ በወረዳዉ ከሚገኙ የተፈጥሮ መስህብ ስፍራዎች አንዱ ነዉ፡፡ በአከባቢዉ ህብረተሰብ በተለምዶ የተለየ ስያሜ ይሠጠዋል፡፡ ይህም የሁሎ ዋሻ/ሳሮ ዋሻ/ ነዉ፡፡ ስያሜዉ ሊገኝ የቻለዉ ከሚገኝበት ቦታ የተነሳ እንደሆነ የአከባቢዉ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ የዋሻዉ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ በሁለት የሁሎ ወንዝ ዳርቻዎችና ኮረብታ ላይ ነዉ፡፡ እንዲሁም በትልቅ “ላሉ” በተባለ ሀረግ፣ ቋጥኝ፣ ድንጋይ የታጀበ ነዉ፡፡ በተራራዉ ዉስጥ ለዉስጥ የሚገባ አንድ መግቢያ በር ያለዉ ሲሆን ቦታዉ ከሁላ መንደር ወጣ ብሎ ይገኛል፡
ዋሻዉ ጥንታዊና የተፈጥሮ ነዉ ከማለት ዉጭ እንዴት፣ መቼና በማን ተገኘና ተሠራ ለማለት ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም ተፈጥሮ ነዉና ጊዜዉም ሆነ ዘመኑ በጥልቅ የሚያመለክት መረጃ የለም፡፡ እንዲሁም ስፋትና ጥልቀቱን በዉል ለመገመት አዳጋች ነዉ፡፡ ነገር ግን ከዛሬ 53 ዓመት በፊት በንጉሰ ነገስት ሀይለስላሴ ዘመን ሁለት ሰዎች ኢብራሂም አማኑ እና አልይ ኡስማን በወጣትነታቸዉ ገብተዉ እንደ ነበር የአከባቢዉ የእድሜ ባለፃጋ ይናገራሉ፡፡ ሌላዉ ሁለቱ ሰዎች ከአዉሬ ጋር እየተጣሉ በባትሪ ከመግባታቸዉ ቀጥሎ አንዳንድ ሰዎች ርቀቱ 3ና 2 ቁርጥ እንደሚሆን ይናገራሉ፡፡ (ሙሄ ሙሳ ዕድሜ 45) ፡፡ ይህ ማለት ከ15-20 ሜትር ድረስ ርቀቱ ይገመታል፡፡ በመሆኑም ጥቂት ቆየት ባሉ አመታት ዋሻዉ ለዱር አራዊቶች መኖሪያነት ያገለግል እንደነበር የአከባቢዉ ህብረተሰብ ይናገራሉ፡፡ (አቶ ኢብራሂም ኢማም፣ ዕድሜ 58)
6. የሁሶ መስጅ
ሁሶ መስጅድ ከወረዳዉ ዋና ከተማ ጨፋሮቢት በ22 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ሁሶ የሚለዉ ቃል የመጣዉ ትልቅ ሰዎች(ሸኮች) ባሉበት ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ አታዉሩ ድምፃችሁን አጥፍታችሁ በኡስስታ አዉሩ ከሚለዉ ነዉ የመጣዉ ይላሉ፡፡ በወቅቱ አህመድ አላዲ የሚባሉ ሸኮች በአካባቢዉ የሚኖሩ ሲሆን ግለሰቡም ለአከባቢዉ ህብረተሰብ በሃይማኖትና በሌሎች ማህበራዊ ኑሮ ደረጃ ትልቅ ትምህርት የሰጡና ትልቅ ሚና የተጫወቱ መሆናቸዉን የአካባቢዉ ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡ በዚህ እንዳለ ግለሰቡም ለህብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንዳለ ከጊዜ በኋላ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ፡፡ ከዚህም በመነሳት የአካባቢዉ ህብረተሰብ በቀብራቸዉ ላይ ቤት በመስራት ቀጥለዉም መስጅድ በመስራት እነሱን ለማስታወስ ያክል የመስጅዱን ስም ሁሶ በማለት ተሰየመ፡፡ ባሁኑ ወቅትም ከ70 አመት በላይ እንዳስቆጠረ ይናገራሉ፡፡ የመስጅዱ አሰራርም ከጠንካራ እንጨቶችና ሳርን በማልበስ እንዲሁም ከመሃሉ ትልቅ እንጨት ያለዉ ሲሆን በተጨማሪም ለመወጠሪያነት 12 እንጨቶች ከዉስጡ በማቆም ተሰራ፡፡ ባሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ ለእምነት መገልገያነት የሚጠቀም ሲሆን በተጨማሪም በረቢዓል አወል ወር ላይ በአመት አንድ ጊዜ መዉሊድ ስነ-ሥረዓት ይከናወንበታል፡፡
|